የገላን እስር ቤት የኦሮሞ ልጆች ማሰቃያ ሥኦል

Share/Qoodi

ፍርድ ቤት የማያውቃት፤ እንዲፈቱ የተወሰነላቸው የኦሮሞ ተወላጆች ለብቻ ተለይተው የሚሰቃዩባት ምድራዊዋ ሲኦል የ”ገላን እስር ቤት”

Gumii Surichoo Layee’tiin !
የሰቆቃው ሰለባ በሆነው ጉሚ ሱሪቾ ለዬ
ትርጉም በጉማ ሳቀታ ገመቹ!!


(ክፍል አንድ)
.
ይህንን እውነተኛ ታሪክ የምጽፈው በእኔ የደረሰውን ሳይሆን የአብይ አህመድ ስርአት ከተመሰረተ ቦሀላ በኦሮሞ ወጣት ቀሬዎች (እንስት እህቶቻችን) ላይ ሲፈጸም የነበረውን እና ዛሬም እየተፈጸመ ያለውን ነው።


.
ሰኔ 15/2021 ከኦሮሚያዋ እንብርት ፊንፍኔ ታፍኜ ተወሰድኩ። ለአስራ ዘጠኝ ቀናት በልደታ ክፍለከተማ ባለ ፖሊስ ጣቢያ ጨለማ ክፍል ውስጥ ስታሰር ከሰው ጋር መገናኘት የቻልኩት አንድ ቀን ብቻ ነበር። ምግብ የሚያቀርቡልኝ ፖሊሶች ናቸው።በሩን ከፈት አድርገው ምግቡን ጣል አድርገውልኝ በሩን በላየ ይዘጉታል።
ፊንፍኔ በታሰርኩበት ወቅት እጆቼ በሰንሰለት በመታሰራቸው እና አጥንቴ ድረስ ዘልቆ ይሰማኝ ስለነበረ ቀኝ እጄ አልታዘዝ ብሎኝ ለሶስት ሳምንት ከፈጠረብኝ ህመም ውጭ በምርመራ ላይ በጥፊ ከመመታት እና ስሜቴን ለመጉዳት ከሚጠቀሟቸው የተለያዩ ስድቦች በቀር የደረሰብኝ የአካል ጉዳት አልነበረም።

ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ለ19ቀን ከታሰርኩ ቦሀላ ድንገት የጨለማው ቤት በር ተከፍቶ ከልደታ ክ/ከተማ እስር ቤት አውጥተውኝ አምስተኛ ተብሎ ወደሚጠራው እስር ቤት ተወስጀ ከሌሎች እስረኞች ጋር ታሰርኩ።
በታሰርኩበት ክፍል ውስጥ ያሉት እስረኞች በሀሺሽ አእምሯቸው የናወዘ፣ነብስ በማጥፋት እና የከፋ ወንጀል የፈጸሙ ታሳሪ ዱርየዎች ሲሆኑ በቋንቋም የምግባባቸው ጭምር አልነበሩም።

ከጥቂት ከቀናት ቦሀላ አሳሪዎቼ ወደ ፍርድ ቤት አቀረቡኝ።የተመሰረተብኝ ክስ “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰራዊት አባል መሆኔን ጠቅሶ ፊንፍኔ ውስጥ መሽጌ ደቡብ እና ምእራብ ኦሮሚያ ላይ ከዳያስፖራ በሚላክልኝ ገንዘብ እየተንቀሳቀስኩ
የመንግስት ባለስልጣናትን ስገድል እንደነበረ እና ድልድይ እና የባቡር መስመሮችን ለማፍረስ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለሁ እጅ ከፍንጅ የተያዝኩ መሆኑን ነው ለፍርድ ቤቱ የተነበበው።

ችሎቱ መልስ እንድሰጥ ሲጠይቀኝ እራሴን እያስተዳደርኩ የምማር መሆኔን በዝርዝር እንደገለጽኩ
ዳኛው የተከፈተብኝ ክስ ተአማኒ አለመሆኑን በማመኑ
“ማስረጃቹ ምንድነው?” የሚል ጥያቄ ለከሳሾቼ ሲያቀርብ
ማስረጃ እያጠናከሩ እንደሆነ ሲገልጹ የዳኛውም መልስ
“ተጠርጣሪውን ከመያዛቹ በፊት ማስረጃችሁን አጠናቅራቹ ነው ተጠርጣሪውን መያዝ የምትችሉት እንጂ ንጹህ ሰው ይዞ ማቅረብ ተቀባይነት የለውም” በማለት መዝገቡን ዘጋው።

ዳኛው እንድለቀቅ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም አልተፈታሁም። ዳግም አስራ ዘጠኝ ቀናት አለፍርድ ቤት ታሰርኩ።በዚህ መካከል ብልጽግና “ምርጫ ” በማለት በጠራበት ሰሞን ችግር ሊፈጥሩብን ይችላሉ ያሏቸውን የኦሮሞ ተወላጆች ማሰር ጀምረው ነበር። ከነዚያ እስረኞች መካከል ከሰራ ቦታቸው ታፍሰው የመጡ ስድስት የኦሮሞ ተወላጆችን አምጥተው ከኔ ጋር ቀላቀሏቸው።ይህ አጋጣሚ ለኔ መልካም ሆነ። ቤተሰቦቼ ያሉት ቦረና ሲሆን ወዴት እንደገባሁ የሚያውቁበት አንዳች መንገድ አልነበረም።
አዲስ ከመጡት የኦሮሞ ተወላጅ እስረኞች ጋር ከተዋወኩ ቦሀላ እነሱን ሊጠይቁ የመጡ ቤተሰቦቻቸው ወደ ቤተሰቦቼ ስልክ ደውለው ያለሁበትን እንዲነግሩልኝ አስደረኩ።

በመቀጠልም በተዘጋ ፍርድ ለምን እንደታሰርኩ እንድጠይቅ በተመከርኩት መሰረት ለምን እንደማልፈታ ጥያቄዬን ለፖሊስ ጢቢያው ተጠሪ አቀረብኩ።የሚገርመው ነገር የጣቢያው ሀላፊዎች እዚህ እንዳለሁም የሚያውቁት ነገር አልነበረም።
እንደ አዲስ “ለምንድነው የታሰርከው፣ማነው እዚህ ያመጣህ” የሚል የተምታቱ ጥያቄዎችን ካቀረቡልኝ ቦሀላ “ለማንኛውም የመታወቂያ ዋስ አቅርብና ውጣ” የሚል ምላሽ ተሰጠኝ።

ቤተሰቤ በቅርብ ባለመኖሩ የግድ ለምርጫ ሰሞን አብረውኝ ታስረው ከተፈቱት ስድስት የኦሮሞ ተወላጆች መካከል የአንደኛውን የስልክ ቁጥር በወረቀት ይዠ ስለነበር አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ፖሊስ እንዲደውልልኝ ተማጸንኩት።

ሁሌም የማመሰግነው ሰው ሙርቴሳ ኢብሮሽ እንደተደወለለት መታወቂያውን ኮፒ አድርጎ ደረሰልኝ።ሙርቴሳ እኔን ለማስፈታት ከአንደኛው ቢሮ ወደ ሌላው እየተሯሯጠ ባለበት የእስር ቤት በር የሚዘጋበት ሰአት ደረሰ ተብሎ እንዳድር ተበየነብኝ።የምለብሰውን ልብስ እና እራት አምጥቶልኝ ነገ በጠዋት እንደሚመጣ ነግሮኝ ተለያየን።
የእስር ቤቱ በር ሲዘጋብኝ ነገ በጣም ራቀችኝ።እድሌን አማረርኩት።ምርጫ አልነበረኝምና እራሴን አሳምኜ ጋደም ብያለሁ። ልክ ከምሽቱ አራት ሰአት ሲሆን የታሰርኩበት እስር ቤት ተበርግዶ ሲከፈት ህልም ያህል ሆኖ ነው የሚሰማኝ።
ከመኝታዬ አካልበው በማስነሳት ንብረትነቷ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በሆነ አምቡላንስ ውስጥ ከተውኝ መኪናዋ ጉዞ ጀመረች።

ከጎኔ የተቀመጡትን የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ዩኒፎርም የለበሱ ወታደሮች ወዴት እየወሰዱኝ እንዳለ ስጠይቃቸው በደፈናው “ኦሮሚያ” የሚል መልስ ብቻ ነው የሰጡኝ።

ንጋት ሳይመጣ ከምወሰድበት መድረስ እንዳለባቸው በተነጋገሩት መሰረት ሹፌሩ በምጥ እየተሰቃየች ያለችን እናት ህይወት ለማትረፍ በሚመስል ማደናገር የድንገተኛ አደጋ ቀይ መብራቱን አብርቶ የአደጋ ድምጽ እያሰማ፣ኬላዎች ቀድመው እያሳለፉት ተሽከርካሪዎች እየቆሙ መንገድ እየለቀቁ አምቡላንሷ ጋለበች።

ያቺ የሰቀቀን የጭንቀት እለት ፈጽሞ አትዘገፈነጋኝም
ሰኔ 18/2021!
ምጥ እንዳጣደፋት እናት እስትሬቸር ላይ በጀርባዬ ታስሬ በጨለማው መካከል በጨለመ ተስፋ ውስጥ ሆኘ የሁለት ሰአት ጉዞ ካደረግን ቦሀላ ድንገት አምቡላንሱ ቆመ።የታሰርኩበት ተፈትቶልኝ ፌስታሌን ይዠ ከመኪናው ስወርድ ድቅድቁ ጨለማ ይበልጥ ጨለመብኝ።
የት እንዳለሁ ለማወቅ አልቻልኩም።አይኖቼን በጭለማው ውስጥ እንደተከልኩ ከአምቡላንሱ በር ፊትለፊት አንድ ነገር ያየሁ መሰለኝ። የባቡር ሀዲድ።
በዚሁ ቅጽበት ደግሞ ከርቀት ወደኛ የሚመጣ የባቡር ድምጽ ተሰማኝ።
ጥቂት እርምጃዎች ብቻ ወደፊት እንደተራመድን አጥሩ ነጭ ቀለም በተቀባ ግቢ ውስጥ አስገቡኝ።
በግቢው ውስጥ አንድ L ሼፕ ቤት እና ለብቻ ደግሞ ከጎኑ በላሜራ (ኮንቴይነር መሰል) የተሰሩ ሰርቪስ የሚመስሉ አራት ክፍሎች ይገኛሉ።
በላሜራ ከተሰሩት ቤቶች በር ላይ ብዛት ያላቸው ጫማዎች ይታዩኛል።ከዛም ውጭ

በተለምዶ አንድ ቁጥር እየተባለ በሚጠራው L ሼፕ ክፍል አስገቡኝ። አራት የኦሮሚያ ፖሊሶች ጋደም ብለው ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ሲሆን አንዱ ከላይ ጃፖኒ በቁምጣ የለበሰ ፖሊስ ከፊትለፊቱ ትልቅ መዝገብ አስቀምጦ ቴሌቪዥን እያየ ነው።ከወሰዱኝ ሁለቱ ፖሊሶች አንደኛው መዝገብ ወደ ያዘው እየወሰደኝ
ሰላምታ ሲለዋወጡ ጎደኛሞች እንደሆኑ አቀራረባቸው ያሳብቅባቸዋል።

መዝገብ ከፊቱ ያደረገው ፖሊስ ገና እንዳየኝ ቀልቡ ጭምር የወደደኝ አይመስለኝም። ብርዱ ከድንጋጤ ጋር ተጣምሮ ጥርሶቼ ይንገጫገጫሉ።
ቦሀላ እንዳረጋገጥኩት መዝገብ ከፊቱ ያስቀመጠው ሳጂን ከተማ ይባላል።

ሳጂን ከተማ ለደቂቃዎች ከላይ እስከ ታች አገላብጦ ከተመለከተኝ ቦሀላ በሚያስደነግጥ ጩኸት “አምጣ ፌስታልህን፣ የያዝከውን ሁሉ አውጣ” በማለት አዘዘኝ። የኪስ ቦርሳ፣ስልክ፣ጫማ ከፊንፍኔ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አጅበው ያመጡኝ ፖሊሶች እጅ ላይ ስለነበረ ፖሊሶቹ አስረከቡ። በፌስታል የያዝኳት አንድ ቲሸርት እና አንድ ጂንስ ሱሪ ሲሆን እሱንም የሰጠኝ በእስር ቤት የተዋወኩት እና ዋስ ሊሆነኝ የነበረው ሙርቴሳ ነው።

ሳጂኑ ስሜን መመዝገብ ጀመረ
ስምህ ?
Gaayoo Khootee አልኩት
ስሜን ለመጻፍ እንደተቸገረ ገብቶኛል
“የአያትህ ስም” አለኝ
“Adii” እንዳልኩት
“ganaa diimatta” አለኝ (አዲ ወደ አማርኛ ስንመልሰው ሁለት ትርጉሞች አሉት። አንደኛው “አጥር” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ነጭ”የሚል ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን ሳጂኑ “ነጭ” የሚለውን ብቻ በመረዳቱ
“ganaa diimatta” “ገና ትቀላለህ ” በማለት እያላገጠብኝ አጅበው ካመጡኝ ተረከበኝ። የቦረና ተወላጅ መሆኔን ስለተረዳ “ጎሊቾ ነው አይደል የላከል” እያለኝ ሌላ ፖሊስ በመጥራት የፖለቲካ እስረኞች ወዳሉበት እንዲያስገባኝ ትእዛዝ ሰጠ።
ወደ መታሰሪያዬ 4ቁጥር እየወሰደኝ ያለው ፖሊስ ሊያረጋጋኝ እየሞከረ
“Ayizoo! Dhiira waan hedduutti mudataa” (አይዞህ ወንድ ልጅ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሙታል” እያለኝ የአራት ቁጥርን በር ከፍቶ አስገባኝ።
ወደ ውስጥ ለመግባት ሰሞክር ከውስጥ የሚወጣው የሙቀት ወላፈን ወደ ሲኦል የተጣልኩ ያህል ይጋረፋል።በጠባቧ ክፍል ውስጥ ሀያ ስድስት ሰዎች ታስረውባታል። ሀያ ሰባተኛ ሆንኩ።

ከውስጥ የእስረኞች አይን እኔ ላይ ተተከሉ። ድንዝዝ ብየ በቆምኩበት አንድ ቀላ ያለ እና በቁመት ከኔ አጠር የሚል ጎፈሬው ያደገ ወጣት “እንኳን ደህና መጣህ አይባልም። ግና እንኳንም ተርፈህ በህይወት ቆየህ” አለኝ። ከቤቱ ሙቀት የተነሳ ከአንድ ሰው በቀር ሁሉም ከላይ ራቁታቸውን ሲሆኑ ፖንት ብቻ ነው የለበሱት።

አንዳንዶቹ ቅማል ይቀማመላሉ፣ሌሎች ተጠጋግተው ያወራሉ። በዚህ መሀከል አይኖቼ በማውቀው ሰው ላይ ተተከሉ። ድንጋጤዬ ጨመረ።አምላኬን ተማጸንኩት “እርሱ እንዳልሆነ” እንዲነግረኝ።
አልተሳካልኝም። እራሱ ነው።በዚህች በተጨናነቀች የሲኦል ተምሳሌት በሆነችው ቤት ያየሁት ስለ ኦሮሞ ህዝብ ሲል የራሱን የተንደላቀቀ ህይወት እርግፍ አድርጎ በመተው ከሰላሳ አምስት አመት በላይ እንደሌሎች ወደ አውሮፓ መሄድ ሳያምረው ከጓዶቹ ጋር ድንጋይ ተንተርሶ የኖረው የኦነግ ሰራዊት አዛዥ የነበረው ጃል አብዲ ረጋሳ ነበር።

ክፍል ሁለት ይቀጥላል

Leave a Reply